ችግሮችን የሚፈታና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ በመንግሥት ግዥ እና ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ለክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና አባላት በእውቀት ላይ ተመስርተው የክትትል ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ሥልጠና እየሰጠ ነው። የክልል ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባላቱ የመንግሥትን የፋይናንስ አስተዳደር እና ግዥ ሥርዓቱን ተገንዝበው በክልሉ ያሉ ባለበጀት መ/ቤቶች የሚመደበውን በጀት በአግባቡና ለታለመለት አላማ መዋሉን ለመቆጣጠር እና ወጭን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር የሚያስችል ስራዎችን ለመመዘን በሚያስችል መልኩ ሰፊ ግንዛቤ እንዲይዙና ችግሮችንም በእውቀት ላይ ተመስርተው ለመፍታት እንዲያግዝ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት በየጊዜው የሚያጸድቀው በጀት በፈፃሚዎች በአግባቡ ለታለመለት አላማ መዋሉን፣ የአሰራር ህግን ተከትሎ እየተመራ ስለመሆኑ መገምገምና መከታተል እንዲያስችል ተጨማሪ እውቀት የፈጠረ ስልጠና ነው የሚሉ አስተያየቶችና የተለያዩ ጥያቄዎች በሰልጣኞች ተነስተው በተነሱበት አግባብ በቢሮ ኃላፊው ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሃናን አብዱ በክልሉ በገንዘብ ቢሮ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለውን ሥልጠና አቅምን የሚያጐለብትና የነበረውን ክፍተት በበቂ ሁኔታ ለመሙላት የተደረገ ጥረትን አድንቀው የፋይናንስ ውጤታማነት ወይም ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት፣ የኦዲት ግኝቶች ላይ ጠንከር ያለ የአሰራር ስርአት መዘርጋትና ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ ለተቋማት የተመደበውን በጀት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን መከታተልና ያለውን ውስን ሃብት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የተሰጠው ስልጠና በቂ ግንዛቤ አስጨብጦናል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሃናን አያይዘውም በክልሉ የተመደበው ውስን ሃብት ለታለመለት አላማ እንዲውል ሁሉም የተቋማት ኃላፊዎችና የክልሉ የም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡