በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶች ተደራሽ እንዲኾኑ የተግባቦት ሥራው እንዲጠናከር የሚጠይቅ መድረክ ተካሄደ።
ባሕር ዳር : ኅዳር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ አዘጋጅነት የፌዴራል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች የክልል ሴክተር መሥሪያ ቤት መሪዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች የተገኙበት በሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶች ዙሪያ የሚመክር መድረክ በባሕርዳር ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ በሰሜኑ ጦርነትና በውስጥ ግጭት ጉዳት የደረሰበት አማራ ክልል በርካታ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው መገንዘባቸውን ገልጸዋል። የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶች በተገቢው መጠንና ፍጥነት ተደራሽ እንዲኾኑ አጋር አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ.ር) አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቀበሌ ድረስ ወርደው ድጋፍ ማድረግ ለጀመሩ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ምሥጋና አቅርበዋል። ተቋማቱ ያደረጉት ድጋፍ ተመሳሳይ ተግባር መፈጸም ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያረጋገጠ ተግባር ነው ብለዋል። መልሶ ግንባታ እና አስቸኳይ ድጋፍ ተከታይነት ያለው እና የቅንጅት ሥራ ይፈልጋል ያሉት የፌዴራል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶች ተደራሽ እንዲኾኑ የተግባቦት ሥራው እንዲጠናከር አሳስበዋል፡