በፈፃሚ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ሲሉ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፤
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የክልል ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሰብሳቢዎች በተገኙበት በመንግስት ግዥና ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) በስልጠናው የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተቋማትን ድጋፍ ሲያደርጉ በበቂ እውቀት ላይ ተመስርተው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ በሚያስችል ሁኔታ በበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ፣በመንግስት ሂሳብ አያያዝና ወጭ አስተዳደር ፣በኦዲት ፣በመንግስት ግዥ፣በውጭ ሃብት እርዳታና ብድር እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አሰተዳደር ዙሪያ የአሰራር ስርዓቱን ተከትሎ መፈጸምና ማስፈጸም አንዲችሉ የስልጠናው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡ የም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት ተረድቶ ድጋፍ ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት የገለጹት ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) እያንዳንዱ ተቋም በጀት ሲያጸድቅ ገቢና ወጭ ተጣጥሞ መሰራት እንዳለበት እዚህ ላይ በየደረጃው ያለን አስፈጻሚዎችን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ትኩረት ሰጥቶ መገምገም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የክልሉን ገቢ መሰረት በማስፋት ተጨማሪ ገቢ በማመንጨት ስራ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊተገበር እንደሚገባም ቢሮ ኃላፊው ጨምሮ ገልጿል፡፡ ዶ/ር ጥላሁን አክለውም እያንዳንዱ ተቋም በጀቱን ሲመራ ወጭ ቆጣቢ በሆነ እና የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ የሞራል ኃላፊነት ወስዶ መፈጸምና ማስፈጸም ይገባል ሲሉ በአንክሮ ገልጸዋል፡፡ የውስጥ ኦዲተሮች ከሙያ አንጻር ነጻ ቢሆኑም መዋቅራዊ ነጻነት ስለሚጎላቸው በዘርፉ ያለውን ችግር በጋራ እየፈቱ ውጤታማ ኦዲት አሰራር እንዲፈጠር ባለድርሻ አከላት እና የም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል ም/ቤት የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሃናን አብዱ በበኩላቸው በተዋረድ ያሉ የም/ቤቱ መዋቅሮቻችን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ቀጣይ የሚወጡ ህጎችን ኦዲት ከማድረግ ጀምሮ እስከ ተጠያቂነት መርህን ያካተተ በአግባቡ ተግባራዊ የማድረግ ስራ የዚህ ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊነት ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡