በእርዳታና ብድር የሚመጣን ሃብት ለታለመለት አላማ ለማዋል ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት ከፍተኛ ሚና ይጠበቃል፡፡
ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ************************* ገንዘብ ቢሮ ለክልል ም/ቤት የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት በሰጠው ስልጠና የእርዳታና ብድር ሃብት ለታለመለት አላማ መዋሉን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በዘርፉ የመጣው ሃብትና እየተከናወነ ያለውን አሰራር ለም/ቤት አባላቱ በውጪ ሃብትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት በኩል እውቀትን ሊያስጨብጥ በሚችል መልኩ የስልጠና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ስልጠና ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) በስልጠናው እንደገለፁት በእርዳታና ብድር የሚገኘውን ሃብት ፈፃሚ ሴክተር መ/ቤቶች እንደመደበኛ በጀት በእቅድ ይዘው ለታለመለት አላማ እንዲውልና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡ በእርዳታና ብድር የሚመጡ ሃብቶችና የሚተገበሩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ሃብት በአግባቡ ለፈፃሚ አካላት በማስተላለፍ፣ የመጣውን ሃብት ለታለመለት አላማ መዋሉን በመከታተልና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ብሎም የስራ ሪፖርቶችን በወቅቱ ለረጅና አበዳሪ አካላት የመላክና ተጨማሪ ሃብት ለማግኘት የሚሰራበትን መንገድ የውጭ ሃብት ግኝት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰብለወርቅ ሙላት በስልጠናው በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አዝመራው ተጫኔ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑና በፈቃደኝነት የተመሰረተ የመንግስት አካል ያልሆኑና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ሆነው ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት የሚሰሩ መሆናቸውን ገልፀው በእነዚህ ድርጅቶች የመጣው ሃብት ለታለመለት አላማ እየዋለ ስለመሆኑ በመከታተልና በመገምገም ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ጥረት እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አቶ አዝመራው ተናግረዋል፡፡