ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች በአማራ ክልል ለደረሰው የሰባዊና ማህበራዊ ቀውስ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠየቀ//
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ መንግስትና የሲቪል ማህበርሰብ ድርጅቶች ጋር በክልሉ ለተከሰተው ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ዙሪያ የሚመክር የአጋርነት መድረክ አካሄደ፡፡ በአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በተፈጠረውና አንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ግጭት ምክንያት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሰብዓዊ ፣ ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መድረሱን በመድረኩ ጥናታዊ ጹሁፍ ያቀረቡት በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ መቋቋምና ግንባታ ፈንድ ፅ/ቤት ስራ አስኪያጅ አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ በክልሉ በተፈጠረው ጦርነት ለደረሰው ሰብዓዊ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግ እና በችግሩ ስፋት ልክ ለአጋር አካላት በማሳወቅ በክልሉ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ውድመት የሚመጥን ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ አለማቀፍና አገር አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጂቶች በአማራ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ለደረሰው ማህበራዊ ፣ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈን አይደለም ያሉት ዶክተር አባተ የአማራ ክልል ሰፊና ብዙ ህዝብ የሚኖርበት ክልል መሆኑን ጠቁመው ረጂ ድርጅቶች ለአማራ ክልል ህዝብ ችግሩን የሚመጥን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶክተር አባተ አክለውም በዓለም ላይ ለጦርነት በትሪሊዮን የሚቆጠር ወጭ እንደሚወጣ ገልፀው ለመልሶ ግንባታ ስራ ግን በትሪሊዮን አይደለም በሚሊዮን እንኳን የሚቆጠር እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ በየትኛውም ዓለም በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም ያሉት ስራአስኪያጁ የኛ ክልልም መጨረሻ ላይ መስማማት ላይ መድረሱ አይቀርምና በመልሶ መቋቋምና ግንባታ ስራውን የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ አሁን ላይ በክልሉ በደረሰው ጉዳት ልክ የሚመጥን ድጋፍ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አሰታውቀዋል፡፡