የሙስና ትግሉ የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተገለፀ፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሰራር ያለቸው ተዛማጅነት በሚል ርዕስ ከቢሮው ሰራተኞች ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡ በፓናል ውይይቱ የተገኙት የገንዘብ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አታለይ ጥላሁን የፀረ ሙስና ትግሉ ውስብስብ እንደሆነ ገልፀው በየጊዜው ትኩረት ሰጥተን ካላረምነው እየሰፋ ስለሚሄድ ለችግሩ የላቀ ትኩረት ሰጥተን በመፈፀምና በማስፈፀም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ልናበረክት ይገባል ብለዋል፡፡ የሙስና ትግሉ የመንግስት ወይንም የአንድ ተቋም /ፀረ ሙስና/ ኃላፊነት ብቻ አይደለም ያሉት አቶ አታለይ ጥላሁን ሙስናን ለመከላከል ሁሉንም ተቋማት ጨምሮ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ኃላፊነት ወስዶ በመስራት ለትግሉ ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አቶ አታላይ አክለውም እንደክልል አሁን ላይ የጋጠመን የፀጥታ ችግር የሙስና ትግሉን ውስብስብ እንዳደረገው ገልፀው ለህብረተሰቡ ተገቢና ወቅታዊ ግንዛቤ በመፍጠር የአመለካከት ለውጥ ከማምጣት ጎን ለጎን የተጠያቂነት ስርዓትም አብሮ ሊተገበር ይገባል ብለዋል፡፡ የፓናል ውይይቱን ያቀረቡት በገንዘብ ቢሮ የስነ ምግባር መኮነን የሆኑት ወ/ሮ ፀሃይነሽ ሙሉ በበኩላቸው ሙስናን ለመከላከል የፀረ ሙስና ተቋም ብቻ አለመሆኑን ገልፀው ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እና ኃላፊነት በመውሰድ ለፀረ ሙስና ትግሉ ወጤታማነት መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ አሁን ያለው የሰላም እጦት በሙስና ትግሉ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት ወ/ሮ ፀሃይነሽ ሙሉ ለዘርፉ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ላይ መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ሙስናን የመከላከል ተግባር የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎና አጋርነት ይጠይቃል ያሉት የፓናል ወይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር ተግባሩን ውስብስብና ለምዝበራውም ጭምር እንደምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡አሁን ላይ የተረሳ የሚመስለውን የፀረ ሙስና ትግሉ የበለጠ ትኩረት በመስጠት የማስተማር ስራን ጨምሮ ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ስረዓት በመዘረጋትና አለፍ ሲልም በህግ ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ጨምረው ገልፀዋል፡፡