የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለደረሰ ውድመት የሚያደርጉት ድጋፍ በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑ ተገለፀ
በአብክመ ገንዘብ ቢሮ በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለተጐዱ አካባቢዎች ድጋፍ ለማድረግ ከመንግስትና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡ በምክክር መድረኩ የተገኙት የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ ዶ/ር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ኮቪድን ጨምሮ በተለያዩ የሰላም ማጣት ምክንያቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትና ብዙ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍልም የችግሩ ሰለባ እንደሆነ አንስተው በዚህም በእለት ደራሽና እርዳታ እንዲሁም በጤናና በትምህርት ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጥላሁን አያይዘውም በዚህ ወቅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁንም ክልሉ ችግር ውስጥ እንደሆነና የአለም አቀፍና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከአሁን በፊት ከሚያደርጉት ድጋፍ በበለጠ ሃብታቸውን አጠናክረውና ተረባርበው የማህበረሰቡን ችግር በሚፈታ መንገድ ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በክልሉ ከደረሰው ጉዳት አንፃር የሚመጥን ድጋፍ ለማሰባሰብና ጉዳቱ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ከማድረግ አኳያ ከዚህ መድረክ በተጨማሪ በክልል ደረጃና በአገር አቀፍ ደረጃም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተጨማሪ የተለያዩ አገራት ኤንባሲዎችና ረጅ ድርጅቶች በተገኙበት የአጋርነት መድረክ እንደሚካሄድም ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የደረሰው የጉዳት መጠን በደንብ መረዳትና ለማህበረሰቡ መረጃ መስጠት እንዲሁም ወደ ስራ ያልገቡ ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደ ስራ በመግባት ክልሉን ከጉዳት ለመታደግ መስራት እንዳለባቸው ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡