በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ውድመት በሰሜኑ ጦርነት ልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተደገፈ አይደለም ተባለ
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ በተፈጠረው ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ ምላሽ ለመስጠት የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ምክክር መድርክ አካሄደ፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አታለይ ጥላሁን በአማራ ክልል የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለውን ወድመት ጨምሮ አሁን በክልላችን ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሰው ሰባዊና ማህበራዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የክልላችን መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ በመቀናጀት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር ከመንግስት በተጨማሪ የሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ም/ ቢሮ ኃላፊው አቶ አታላይ የልማትና መልሶ ማቋቋም ስራው ጋር አቀናጅቶ ለመስራት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት የደረሰበትን ጉዳት ገና ሳያገግም አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠረው ተጨማሪ ችግር ሆኖብናል ያሉት አቶ አታላይ በአለም ላይ ሰባዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች በችግር ወቅት ገብተው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀው አሁን ላይ ክልላችን ካጋጠመው ችግር አንጻር ችግሩን ድጋፍና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በችግር ወቅት አጋርነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ማህበራዊና ሰባዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት አሁን ገንዘብ ቢሮ እየሰራ ባለበት ሁኔታ በክልል በርዕሰ መስተዳድር ደረጃ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ረጅ ድርጅቶች በተገኙበት ተመሳሳይ የአጋርነት መድረክ በመፍጠር የድጋፍ ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡ በክልሉ የደረሰውን ሰባዊ ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የጉዳት መጠን በደንብ በመረዳት ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ መስጠት እንደሚገባ የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊዎች አማራ ክልል ላይ እየተሰጠ ያለው ምላሽ አናሳ ስለሆነ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳቱ መጠን ልክ ግልፅ መረጃ በመስጠት ደጋፍ ማሰባሰብ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ግጭት በየትኛውም አለም እንዳለ የገለፁት ተሳታፊዎች በአማራ ክልል በደረሰው ጉዳት ልክ የረጅ ድርጅቶች ምላሽ ከሰሜኑ ጦርነት አንፃር ሲታይ ዝቀተኛ እንደሆነ በመግለፅ የታሪክ ተጠያቂ እንዳንሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታችነታችንን እንወጣ ሲሉ አሳስበዋል፡፡