የእርዳታና ብድር ሃብት አጠቃቀም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል
የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ከፈፃሚ ሴክተር መ/ቤት ኃላፊዎችና የፕሮጀክት ባለሙያዎች እንዲሁም ከእርዳታና ብድር ፕሮጀክትቶችና ፕሮግራሞች አስተባባሪዎች ጋር የእርዳታና ብድር የሃብት አጠቃቀምን ገምግሟል፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን በግምገማው እንደገለፁት ለክልሉ ከሚመደበው መደበኛ በጀት በተጨማሪ በእርዳታና ብድር ሃብት እንደሚመጣና ይህንን ሃብት የመጣለትን አላማ አውቆና በአግባቡ ይዞ ከመጠቀም አኳያ ከፈፃሚ ሴክተር መ/ቤቶች የትኩረት ማነስ እንዳለ ገልፀው ይህንን ክፍተት በመለየት በቀጣይ የተሻለ አሰራር በመፍጠር እንዲሁም የተሻለ የሃብት አስተዳደር እንዲኖር ታስቦ የተዘጋጀ ግምገማ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ክልሉ አሁን ካለበት ችግር ውስጥም ሆኖ በእርዳታና ብድር በሚመጣው ሃብት እየተሰራ ያለው ስራ ጥሩ ነው ያሉት አቶ አታለይ ከዚህ በተሻለ በመስራትና እንደመደበኛ በጀት ሁሉ በእቅድ ይዞ ለታለመለት አላማ ማዋልና የጠራ መረጃ በመያዝ፣ ግልጽና አጭር ሪፖርት በወቅቱ በመላክ ተጨማሪ ሃብት በማምጣት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በግምገማው በገንዘብ ቢሮ አጠቃላይ የሴክተሮች አፈፃፀምና ከፈፃሚ ሴክተሮች ውስጥ የአብክመ መስኖና ቆላማ ቢሮ፣ የአብክመ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮና እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ሪፖርታቸውን ለውይይት አቅርበዋል፡፡ በአብክመ ገንዘብ ቢሮ የውጭ ሃብት ግኝት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰብለወርቅ ሙላት በእርዳታና ብድር የሚመጣን ሃብት ፈፃሚ ሴክተር መ/ቤቶች ለተባለለት አላማ በመጠቀም በአሰራር የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍትሔ በማበጀት የተሻለ ሃብት ለማምጣት ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡