NEWS DETAIL

News on 'ተቋማት በኦዲት የተገኘባቸውን ጉድለት እንዲያርሙ ተጠየቀ።'

ተቋማት በኦዲት የተገኘባቸውን ጉድለት እንዲያርሙ ተጠየቀ።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ግኝት ካለባቸው ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል። ለሦስት ቀናት በተደረገ ውይይትም የተቋማት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ቀርቧል። የተገኙ ጉድለቶችን ለማስተካከል የተሠሩ ሥራዎች፣ ከአቅም በላይ የኾኑ እና ሌሎች ችግሮችም ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ በቋሚ ኮሚቴው የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያቀረባቸውን የኦዲት ግኝት በመከታተል የከፋ ጉድለት አለባቸው የተባሉትን ተቋማት በማወያየት ርምጃ ወስደው እንዲያስተካክሉ ለማድረግ መኾኑን ገልጸዋል። ውይይቱ የአሠራር ግድፈት እንዲስተካከል እና የኦዲት ግድፈትን ርምጃ ወስደው በቀጣይም አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትን ለማስፈን ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል። ጉድለት ኖሮባቸው በክትትል የታዩ እና በከፋ የኦዲት ግኝት የታዩ ተቋማትም መኖራቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ኀላፊዎቻቸው ባሉበት የሚታዩ ተቋማት መኖራቸውን ተናግረዋል። ተቋማቱ የፋይናንስ ሥርዓትን ተከትለው እንዲሠሩ፣ ጉድለቶችን አስተካክለው እንዲያሳውቁ፣ የአሠራር ሥርዓቶችን እንዲያስተካክሉ፣ በጉድለት የተገኙትን ርምጃ እንዲወስዱ፣ ይህንን የማያስተካክሉ ከኾነ በሕግ ተጠያቂ እንደሚኾኑ በውይይቱ መገለጹን አንስተዋል። በክልሉ ተሠብሣቢ ሃብት ወደ 17 ቢሊዮን እና ተከፋይ ደግሞ 15 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት ምክትል አፈ ጉባኤው ዓላማው የፋይናንስ ግልጸኝነትን በመተግበር ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ የሚሠበሠበው ገንዘብ ታውጆ ለልማት እንዲውል፣ ተቋማት የመንግሥትን አሠራር እንዲያከብሩ ለማስቻል ነውም ብለዋል። የቋሚ ኮሚቴው ውይይትም ተቋማት በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ አስተካክለው እና ርምጃ ወስደው ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙንም ገልጸዋል። ቋሚ ኮሚቴው የተቋማትን የኦዲት ግኝት ለማስተካከል በሚያደርገው ክትትል እና ቁጥጥር ምክር ቤቱም ብልሹ አሠራር እንዲስተካከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እመቤት ከበደ ባለፉት ሦስት ቀናት ከክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መነሻነት የ12 ተቋማትን የኦዲት ሪፖርት በምክር ቤቱ የአስረጂዎች መድረክ መገምገሙን ገልጸዋል። በመድረኩ የከፋ የኦዲት ግኝት ያለባቸው እና በክትትል የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት በሚል በሁለት ደረጃ መፈረጁንም ጠቅሰዋል። ስድስት ተቋማት የከፋ የኦዲት ግኝት እንደታየባቸው እና ቀሪዎቹ ደግሞ በክትትል የኦዲት ግኝት መካተታቸውን ተናግረዋል። የቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዋ ቋሚ ኮሚቴው ከተቋቋመ ዓመት ያልሞላው መኾኑን እና ከዚያ በፊት ሥራው ይሠራ የነበረው በኦዲት አስመላሽ ግብረ ኀይል እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ራሱን ችሎ ኮሚቴ ተቋቁሞለት በትኩረት እየተሠራበት መኾኑንም ጠቅሰዋል። አብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች በየዓመቱ እየተንከባለሉ የተከመሩ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። በተለይም ተከፋይ እና ተሠብሣቢ የኦዲት ግኝት በክልሉ የፋይናንስ ሥርዓቱን እያዛባ መኾኑንም ተናግረዋል። በየዓመቱ እየጨመረ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ስለኾነም ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት በመከታተል ለማስተካከል እንደሚሠራ ገልጸዋል። በአስረጂ መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዋ ግኝት ያለባቸው ተቋማት በፍጥነት አስተካክለው ለቋሚ ኮሚቴው እና ለክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙን ገልጸዋል። ከዚያ ካለፈም ለሕግ ተጠያቂነት ወደ ሕግ ተቋማት እንደሚተላለፍ አስረድተዋል። የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ሰውበሰው ብዟየሁ መሥሪያ ቤታቸው መንግሥት በየዓመቱ የሚመድበው ሃብት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ኀላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል። ለምክር ቤቱ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ መኾኑንም ተናግረዋል። በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መንግሥት የመደበላቸውን ሃብት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሥራ ላይ ያላዋሉ ጉልህ፣ መሠረታዊ ግኝቶች የተገኙባቸው እና የማጭበርበር ተንኮል ሊፈጸም የሚችልባቸውን አጥጋቢ አይደለም የሚል የኦዲት አስተያየት የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል። መንግሥት የመደበውን ሃብት እንዴት እንደተጠቀሙ ማስረጃ ማቅረብ ያልቻሉት እና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው ስድስት ተቋማት መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኀላፊነት የኦዲት ግኝቶችን ለምክር ቤቶች እስከማቅረብ ድረስ መኾኑን ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የሚያስተላልፈውን አቅጣጫ እና ውሳኔ የሚያስፈጽም የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴው ግኝቶችን ተከታትሎ እንዲስተካከሉ፣ እንዲታረሙ እና የሕዝብ ሃብት እንዲመለስ ይሠራልም ብለዋል። ዋና ኦዲተር እየተከታተለ መረጃዎችን ማቅረብ እና አስረጂ መኾን ነው ብለዋል። የባከነ ገንዘብን በማስመለስ በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ እና አሁን ላይ ግን መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አሠራር መጀመሩን ነው አቶ ሰውበሰው የገለጹት። በኦዲት የተገኙ ጉድለቶች መመለስ የሚገባቸው ሃብቶች እንዲመለሱ ተባብረን እንሠራለንም ብለዋል። በተደረገው የኦዲት ግኝት መመለስ ያለበት በርካታ ሃብት መኖሩን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኦዲተሩ የ2014 በጀት ዓመት የተጠቃለለ የኦዲት ሪፖርት ላይ በክልሉ 17 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተሠብሣቢ ሂሳብ ክምችት መኖሩን በአብነት አንስተዋል። 15 ቢሊዮን ብር ተከፋይ ክምችት መኖሩንም አክለዋል። ይህ ክምችት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን እና የፕሮጀክት አሥተዳደር ሥራ መዳከምም ለመጨመሩ አንድ መንስኤ እንደሚኾን ጠቁመዋል። ማስረጃዎች ማግኘት ያልተቻለበት የተቋማት የኦዲት ግኝት መኖራቸውንም ነው አቶ ሰውበሰው የገለጹት። ቋሚ ኮሚቴው ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች እና ከምክር ቤቱ መሪዎች ጋር በመኾን የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት እንዲያስተካክሉ፣ የሚመለሰው እንዲመለስ፣ ርምጃ እንዲወሰድ እና በሕግ መጠየቅ ያለበትም እንዲጠየቅ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

Recent Posts

በአማራ ክልል የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመ…
Feb. 19, 2025
# በሶስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን የ33 ሚ…
Feb. 19, 2025
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ከፕሮጀክቶች ከዕቅድ…
Feb. 19, 2025
የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግር ያለበት ስ…
Feb. 5, 2025
የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት እርምት እንዲወ…
Feb. 5, 2025
የእርዳታና ብድር ሃብት አጠቃቀም ትኩረት ተሰ…
Feb. 5, 2025
በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ያለ…
Feb. 5, 2025
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ በሰው ሰራ…
Feb. 5, 2025
የሙስና ትግሉ የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ እን…
Feb. 5, 2025
ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች በአማራ ክልል ለደ…
Feb. 5, 2025
በእርዳታና ብድር የሚመጣን ሃብት ለታለመለት አ…
Feb. 5, 2025
በፈፃሚ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት ተግባ…
Feb. 5, 2025
ችግሮችን የሚፈታና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስ…
Feb. 5, 2025
የአማራ ክልል ምክር ቤት የተቋማትን ፋይናንስ …
Feb. 5, 2025
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ለክልል ም/ቤት ቋሚ…
Feb. 5, 2025
በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶ…
Feb. 5, 2025
#ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ ኦረንቴሽ…
Feb. 5, 2025
The 2017 budget program has s…
June 19, 2024