የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት እርምት እንዲወስዱ የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ አሣሠበ፡፡
ደሴ: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ የከፋ የኦዲት ግኝት አለባቸው ያላቸውን ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን በቀጣይ መደረግ በሚገባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ በኮምቦልቻ ከተማ ምክክር አድርጓል። ቋሚ ኮሚቴው የቃሉ ወረዳ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ እና የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የኦዲት ግኝቶች ላይ ትኩረት አድርጓል። ለረጅም ጊዜ እየተንከባለለ የመጣ መሠብሠብ የነበረበት ገቢ መኖር እና መረጃ አለመስጠት ዋነኛ ችግሮች መኾናቸውን የየተቋማቱ የሥራ ኀላፊዎች በምክክሩ ተናግረዋል። የኦዲት ግኝቶችን የማስመለስ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ኀላፊዎቹ ምክር ቤቱ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ በክልል ደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸውን ችግሮች ለማቅረብ ምቹ ኹኔታን እንደፈጠረላቸውም አመልክተዋል፡ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ደሴ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በወንጀል የተገኘ ሐብት ማስመለስ የሥራ ሂደት ተጠሪ ይርጋ ደመቀ የሚሰጡ ጥቆማዎችን በማጣራት ጉድለት የፈጸሙ አካት ተጠያቂ እንድኾኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እመቤት ከበደ ውይይት በተደረገባቸው በሦስቱ ተቋማት እና በሌሎች በክልሉ የመንግሥት ተቋማት የኦዲት ግኝት መሠረት የተሰብሳቢ እና ተከፋይ የኦዲት ግኝት የክልሉን የፋይናስ ሥርዓት እያዛባ በመኾኑ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል። ግኝት ያለባቸው ተቋማትም በግኝቱ መሠረት እርምት ወስደው ግብረ መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሰብሳቢዋ ጉድለቱ ካልተስተካከለ የጥቆማ ኦዲት ተደርጎ ወደ ግለሰብ እንዲወርድ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንዲኾኑ ይደረጋልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡ አሚኮ