የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ከፕሮጀክቶች ከዕቅድ በላይ ሀብት ማግኘቱን አስታወቀ።
ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የስድስት ወራት ሪፖርት ገምግሟል። በዚህም የገንዘብ ቢሮ አፈጻጸም ቀርቧል። የቢሮውን ሪፖርት ያቀረቡት የቢሮው ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) ከፌዴራል፣ ከውስጥ ገቢ፣ ከእርዳታ እና ሌሎች ገቢዎች የሚገኘው በጀት ተደልድሏል ብለዋል። የተመደበውን በጀትም ከፌዴራል እስከ ወረዳዎች በየደረጃው የማስተላለፍ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ከመንግሥት ግምጃ ቤት ከተመደበው መደበኛ በጀት 32 ነጥብ 19 ቢሊዮን ብር ወጭ ኾኖ ሥራ ላይ ውሏል። ለ77 ከተማ አሥተዳደር እና ለ138 መሪ መዘጋጃ ቤቶች 1 ቢሊዮን 458 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ተናግረዋል። ወረዳዎች በጀታቸውን በአይቤክስ በመመዝገብ የማጠቃለል ሥራ 98 በመቶ ፈጽመዋል። ብድር የወሰዱ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በሙሉ ብድራቸውን መልሰዋል። የ28 ባለፕሮጀክት ቢሮዎችን የካፒታል በጀት አፈጻጸም የመከታተል እና የመደገፍ ሥራም ተሠርቷል። ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከ3 ነጥብ 02 ቢሊዮን ብር ውስጥ 0 ነጥብ 653 ቢሊዮኑ ገቢ ተደርጎ ለተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች ተላልፏል። የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት በጀትም ለ82 ወረዳዎች መተላለፉን ጠቅሰዋል። በእርዳታ እና ብድር የተገዙ ቁሳቁሶች ለተጠቃሚ ተቋማት መገዛታቸውንም ገልጸዋል። ወደ ክልሉ ከሚገቡ አራት ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ ተለይተዋል። ከቀረቡ 135 አዲስ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ123 ፕሮጀክቶች ጋር ስምምነት መደረጉን እና ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች አምስት ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መገኘቱንም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥራዎችን ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረ መልሶች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።