በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ለደረሰው ጉዳት መልሶ ግንባታ የአጋር አካላት ድጋፍ ተጠየቀ።
በአማራ ክልል በደረሰው የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጉዳት በዘላቂነት ለመቋቋምና መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ምክክር የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የእርዳታና ብድር ሰጪ ተቋማት ኃላፊዎች እና ሌሎች አጋር አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሄዷል። በምክክር መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ አረጋ ከበደ መድረኩ ክልሉ አሁን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በግልጽና በተጨባጭ መረጃ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ በክልሉ ጉዳቱ ለደረሰበት ህዝባችን የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እና የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የምክክር መድረኩን ወሳኝነት ተናግረዋል። በክልሉ በተፈጠረው ጦርነት በሰብዓዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መውደቁን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው ግጭትም ጉዳቱን ያባባሰ ትልቅ ፈተና መሆኑን አንስተዋል። ክልሉን መልሶ ለመግባት፣ በዘላቂነት ለማቋቋም እና ሰላሙን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ቁርጠኙነቱን ገልፀው በዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች እና የአጋር አካላትን ድጋፍ በፊት ከነበረው የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ክልሉ ከገባበት ሰብዓዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲወጣ በትብብር እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በአንክሮ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሀሪ(ዶ/ር) ክልሉ ባለፉት አመታት ኮቪድን ጨምሮ በሰላም ማጣት ምክንያቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት እና ብዙ ቁጥር ያለው ማህበረሰብም የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ አንስተዋል። በክልሉ የመልሶ መቋቋምና ግንባታ ስራው ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው የክልሉ መንግስት በእለት ደራሽ እርዳታ፣ በጤናና በትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ ስራ በጀት መድቦ ከመስራት ባለፈ ከፌደራል መንግስትና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ሲሰራ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው ከችግሩ ስፋት አንፃር ይህ በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል። ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጥላሁን መሀሪ አያይዘው በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ መቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት፣ በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣ በዩኒሴፍ እና ገንዘብ ቢሮ በቀረበው ሪፖርቶች በክልሉ የደረሰውን የጉዳት መጠን በሰፊው አጋር አካላት እንዲገነዘቡት እና በዚህ ልክ ተረድተው በክልሉ የሚሰሩ የአለም አቀፍ የልማት ድርጅቶችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተገቢና ለውጥን የሚያመጣ ድጋፍ በማድረግ ማህበረሰባችንን ከችግር እናውጣ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።