#ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ ኦረንቴሽን አካሄደ
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት መድረክ ከዞንና ሪጅኦፖሊታን ከተማ አሰተዳደሮች ጋር ገምግሟል፡፡ በቢሮው የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ በኩል የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ከቀረበው እቅድ በመነሳተም በመድረኩ ተሳታፊዎች በኩል ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ደይሬከተሮች መልስና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አዱኛ ክልሉ ካለበት የጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖም ቢሮው እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ በየወሩ ደመወዝ መክፈልን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከሰነድ ክምችት ጋር በተያያዘ የማዕከላዊ ጎንደር ዞንን ተሞክሮ መውሰድ ይገባል ያሉት ም/ቢሮ ኃላፊዋ ከድጋፍና ክትትል ጋር በተያያዘ ለተነሱት ሃሳቦች አካባቢው አንፃራዊ ሰላም እስኪኖር መታገስ እንደሚገባና ከጡረታ ዋስተና አንጻር ወረዳዎች ትክክለኛውን መረጃ መስጠትና ተገቢውን ክትትል ማድረግ ይገባል ሲሉ ወ/ሮ መሰረት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው የ2017 እቅድ እንዲሳካ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት በማድረግ ተግባሮቻችንን በወቅቱ በመፈፀም ሃብትን በአግባቡ እና ለታለመለት አላማ ብቻ በማዋል መፈጸምና ማስፈጸም ይገባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ጥላሁን አክለውም እያንዳንዱ ወረዳ የጡረታ ዋስትና ምን ያህል እንደሆነ ተገቢውን መረጃ በማጣራት መስራት እንደሚገባና የመንግስት ሃብት ያለአግባቡ እንዳይባክን መጠንቀቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከባንክ አካውንት ጋር በተያያዘ ዞኖች፣ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች ገንዘብ ቢሮ ሳይፈቅድ መክፈት እንደማይቻል ቢሮ ኃላፊው የገለጹ ሲሆን ተሸከርካሪ ማስወገድ ጋር በተያዘ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በትክክል መወገድ የሚገባቸውን ተሸከርካሪዎች ለይተን መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ በበጀት ያልተደገፉ መዋቅሮችና የደረጃ ማሻሻያዎች ሲመጡ ቢሮው ጋር እየተነጋገርን መፍታት ይገባል ያሉት ዶ/ር ጥላሁን ከመዋቅራዊ አደረጃጀት አንፃርም እንደ አንድ ፓይሌት ተይዞ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጀምሮ እየተሰራ ስለሆነ በየደረጃው ተጣጥሞ ይሰራል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በክፍተት ያየናቸውን ቀጣይ ስድስት ወር ዳግመኛ ክፍትት መሆን እንደሌለባቸው ኃላፊው አሳስበው ቀጣይ በውጤት እንደምንገናኝ በመጠቆምና መልካም የስራ ዘመን በመመኘት መድረኩን አጠቃለዋል፡፡