የማህበዊ ተጠያቂነት ፕሮግራምን በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል // አብክመ ገንዘብ ቢሮ
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም አተገባበር ዙሪያ ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ተቋማት እና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድረጓል፡፡ በውይይት መድረኩ የተገኙት የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ም/ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደራጀው ካሴ ገንዘብ ቢሮ ከሚያስተባብራቸው ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በክልላችን በ14 ወረዳዎች እና በስራቸው በሚገኙ ቀበሌዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ የገለጹ ሲሆን ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ዜጎችን በማሳተፍና አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ተደራሸ በማድረግ አገልግሎት የሚሰጠው አካል ሲያጎድል የሚጠየቅበት፤እንዲሁም አገልግሎት ሰጭውንና አገልግሎት ተቀባዩን ማህበረሰብ የበለጠ በማቀራረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድረሻ አካላት አፈጻጸሙን በመገምገምና በመደገፍ አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን፣ምቹና ተደራሽ እንዲሆን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ም/ቢሮ ኃለፊው አቶ አደራጀው አሳስበዋል፡፡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የሴቶች ፣ህጻናት፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበረሽ ታደሰ በበኩላቸው የፋይናንስም ሆነ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ስራዎች በክልላችን ሲተገበሩ እንደነበርና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ሲያደረጉ መቆየታቸውን በመግለጽ በፕሮግራሙ መተግበር የሚገባቸው አገልግሎቶች በመንግስትና በማህበረሰቡ የጋራ ተሳትፎ የእድገት ተኮር ተቋማት ጋር በመነጋገር ለህብረተሰባችን ተጠቃሚነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ማህበረሰቡንና መንግስትን በማቀራረብ ልማትን በማፋጠን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም አንደሆነ ወ/ሮ አበራሸ አክለው ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አዱኛ በፕሮግራሙ ጠያቂና መልስ ሰጭ ማህበረሰብ መፍጠር ሲባል ሁሉንም ነገር መንግስት የሚሰራው ሳይሆን ማህበረሰቡም ተሳታፊ ሆኖ የሚሰራበት ስርዓት ነው ብለዋል፡፡የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ተገቢ አገልግሎት በመስጠታችን የምንመሰገንበት፤ አገልግሎቱን ስናጓድል ደግሞ የምንጠየቅበትን አሰራር የሚያጎለብት ፕሮግራም ነው ሲሉ ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል፡፡ ለፕሮግራሙ ውጤታማነት የህብረተሰቡን ፍላጎት በመለየት እና ተገቢ የሆነ እቅድ ይዘን ሁላችንም ባለድርሻ አካላት በጋራ እየደገፍን መስራት ይጠበቅብናል በማለት ም/ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የአማራክልል ምክር ቤት ም/ አፈ ጉባኤና የቋሚ ከሚቴ ሰባሳቢዎች ፣የፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች፣ እንዲሁም የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ተቋማትና ክልል ቢሮ የፕሮግረሙ አስተባባሪዎች ተገኝተው ማብራሪያና የቀጣይ ጊዜያት የስራ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል ፡፡