ቢሮው የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለመገንባት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የጀመረውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ስራን እንደተቋም ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ቢሮው የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እንደተቋም ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር የቀጣይ ጊዜ አቅጣጫ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን የምንፈልገውን ዲጂታል ተቋም ለመገንባት ከወዲሁ ትኩረት ሰጥተን አስበን መስራት ይገባል ያሉ ሲሆን ዲጂታል ንብረት አስተዳደር፣ ዲጂታል የሰው ሃብት አስተዳዳር/HRM/፣ ከኦዲት አስተዳደር እና በመሳሰሉት ዙሪያ በ2019 ዓ.ም እንደተቋም የሚሰሩ ስራዎችን የላቀ ትኩረት ሰጥቶ መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡ ከህግ ማዕቀፍ አኳያ ከገንዘብ ቢሮ አንፃር በማክሮና በማይክሮ ደረጃ ሊተገበሩ የሚገባቸው ተግባራትን ከወዲሁ በመለየት በአግባቡ አስቦ መስራት ይገባል ያሉት ቢሮ ኃላፊው አቶ አታላይ ጥላሁን ከቴክኖሎጅ ጋር የተናበበ እና የተሳሰሩ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት ለቀጣይ 3 አመታት ምን ሊሰራ እንደሚገባ አቅጣጫ እያስቀመጡ መፈፀም ይገባል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ውይይት መድረክ የተነሱ ሃሳቦችን አደራጅተን በመያዝ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ አይቀሬ ስለሆነ ለዚህ አሰራር ምቹ ሁኔታ እየፈጠርን ወደተግባር በመግባት መፈፀም እንደሚገባም ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ እንደተቋም በዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ግንባታ በተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ ስርዓት፣ የተቀናጀ በጀትና ወጭ አስተዳደር፣ የትራንስፖርት ስምሪት መተግበር፣ የበጀት ቀመር፣ ሲማድ፣ የውጭ ሃብት፣ ትሬዥሪ እና ኦዲት የስራ ክፍሎችን ዲጂታላይ ማድረግ፣ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት መተግበር፣ የዲጂታል ሲቪል ሰርቫንት አቅም መገንባት፣ የመረጃ ደህንነት መጠበቅ፣ በተቋሙ የውስጥ አቅም የለሙ የግዥ፣ የንብረት አስተዳደርና የሰው ሃይል ሲስተሞችን በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የቢሮውን ድረገጽ በማዘመን ተደራሽና ዘመናዊ ማድረግ በውይይት መድረኩ የተመከረባቸው ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡