ፕሮግራምን መሠረት በአደረገው የበጀት አመዳደብ ሥርዓት ዙሪያ ሙያዊ ውይይት ተደረገ
የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ከፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር ከመጡ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በክልሉ ፕሮግራምን መሠረት በአደረገው የበጀት አመዳደብ ሥርዓት አሰራር ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን የገንዘብ ሚኒስቴር ክልሉ በአጠቃላይ ፕሮግራምን መሠረት ያደረገው የበጀት አመዳደብ አሰራር የሄደበትን ርቀት ለመገምገምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለቀጣይ ስራዎቻችን በተግባባንበት ልክ የስራ አቅጣጫ ለይተን ወደ ተግባር የምንገባ ይሆናል ብለዋል፡፡ ክልሉ ከላይን አይተም የበጀት አመዳደብ ሥርዓት ወደ ፕሮግራምን መሠረት ያደረገ የበጀት አመዳደብ ገብቶ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረውን አፈፃፀም በገንዘብ ቢሮ በኩል ቀርቦ ለውይይት መነሻ በማድረግ ውይይቱ የተካሄደ ሲሆን የፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴርም ፕሮግራምን መሠረት በአደረገው የበጀት አመዳደብ ዙሪያ እየሰራበት ያለውን ሂደት ለአሰራር ምቹ እንዲሆን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ በፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴር የፐብሊክ ፋይናንስ ሪፎርም አስተባባሪ አቶ ዳዊት ሽመልስ ክልሉ ይህን ፕሮግራም በጀቲንግ ስራ እያከናወነበት ያለውን ሂደት አድንቀው ይህንን በመንግስት የሚመደበውን ውስን ሃብት ለዜጐች ተጠቃሚነት እንዲውል ከዚህ በላይ መስራት እንደሚጠበቅ በመግለጽ ሚኒስቴር መሰሪያቤቱ ሁሌም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል፡፡ በማጠቃለያም የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን የተደረገው ውይይት የተሻለ ተግባር መፈፀም የሚያስችል እውቀት ያገኘንበት ነበር ብለው አፈፃፀሙን በመገምገምና ጥንካሬዎችን ይዘን ክፍቶችን በመሙላት የተሻለ ስራ እንድንሰራ ያግዘናል በማለት አደማድመዋል፡፡