#የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበጀት ዓመቱ 50 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበስብ አስታወቀ፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ አደረገ፡፡ በመድረኩ የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁንን ጨምሮ ሁሉም የም/ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሚመለከታቸው ዳይሬክተሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን አዲስ ተቋም ሲመሰረት ፈተና እና እድሎችም እንዳሉት የገለጹት ቢሮው ኃላፊው አቶ አታላይ ጥላሁን በሚፈለገው ደረጃ ተገቢ ስራ በመስራት ጠንካራ ተቋም መገንባት እድል እንደሚሆን በማስታወቅ የተቋቋመውን ተቋም በአግባቡ በማደራጀት ውጤታማ እንዲሆን ከወዲሁ አስቦ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ተሳትፎ በ6 ዓለማዎች ላይ ተመስርቶ የሚሰራ እንደሆነ የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው አቶ አታላይ ጥላሁን ልማት በመንግስት ብቻ ስለማይመጣ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እና የልማቱ ባለቤት በማድረግ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ 50 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅድ የተያዘ ሲሆን እቅዱ የታሰበውን ግብ ያሳካ ዘንድ ህብረተሰቡ የተሻለ የሚጠቅመውን የልማት ስራ መርጦ እንዲሰራ በማድረግ፣ ህበረተሰቡን በአግባቡ በማሳመንና በማሳተፍ መስራት እንደሚገባም አቶ አታላይ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ አቶ አታላይ አክለውም የእቅዱን ግቦች ለማሳካት የምንከተላቸውን የማስፈጸሚያ ስልቶች በአግበቡ በመያዝ ወደ ስራ መግባትና የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ስራን በአግባቡ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ለክልላችን ህዝብና ለሚመለከታቸው አጋር አካላት ተገቢ ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ አፈጻጸም እንዲኖር ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት ለክልላችን ልማት መስራት ይገባል ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ያየህ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመትን እቅድ ትውውቅ አቅረበው ያስገመገሙ ሲሆን በመድረኩ በተሰጠው ግብዓት መሰረት እቅዱን የበለጠ በማጠናከር ተዘጋጂቶ ለዞኖችና ወረዳዎች ጭምር በማውረድ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፤ሁሉም የክልሉ ህዝብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ውጤታማነትና ስኬት የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡