ስልጠናው አቅምን የሚገነባና ክህሎትን የሚያዳብር መሆኑ ተገለፀ
የአብክመ ገንዘብ ቢሮ በአዲሱ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 306/2018 እና ይህንን አዋጅ ተከትሎ በወጡ መመሪያዎች እንዲሁም በሌሎች የስታንዳርድ ዶክመንቶችን ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ሰልጣኞች ወደ ስልጠና ሲገቡ የመግቢያ ፈተና በመውሰድ ስልጠናውን የጀመሩ ሲሆን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ እና መመሪያዎች ዝግጅት ቢሮውና የተቋቋመው ኮሚቴ የሄደበትን ርቀት መነሻ በማድረግ ከክልል እስከታችኛው እርከን ድረስ የተለያዩ አጋር አካላት ውይይት ተደርጐ ግብአት በማሰባሰብ የተዋጣለትና ደረጃውን የጠበቀ አዋጅና ረቂቅ መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 306/2018፣ በግዥ መመሪያ፣ በንብረት መመሪያና ሌሎች ስታንዳርዶች ዙሪያ በጥልቀት በቡድን ስራ የታጀበ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስለሥልጠናዉ አስተያየት የሰጡ ሰልጣኞች እንደገለጹት ገንዘብ ቢሮ በዚህ ልክ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ አዋጅና መመሪያዎችን እንዲሻሻሉ መስራቱ ሊያስመሰግነው ይገባል፣ ስልጠናው የተሰጠበትና የመግቢያም ሆነ የመውጫ ፈተና መሰጠቱ ምን ይዘን መጥተን ምን ይዘን ሄድን የሚለውን ራሳችንን ያየንበት ነበር፣ የመደማመጥና የመማማር ክህሎታችንን ያዳበርንበት ስልጠና ነው፣ በየቀኑ የምንተገብራቸውን ተግባራት በጥልቀት የዳሰሰ ስልጠና ነበር ብለዋል፡፡ በስልጠናው ማጠቃለያ የተገኙት የአብክመ ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን ለ15 አመታት የቆየው አዋጅና መመሪያዎች አሻሽሎ ወደ ስራ መግባት አንዱ የሪፎርሙ ማስተግበሪያ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን አዋጅና መመሪያ ፈፃሚው አውቆና ተገንዝቦ ወደ ተግባር እንዲገባ ስልጠናው መሰጠቱን በመግለጽ በስልጠናው የተሰጡ የምዘና ፈተናዎች እራሳችንን እንድናይበትና ክፍተቶችን እንድንሞላበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ተቋም የሚገነባው በሁሉም ሰው ተሳትፎ ሆኖ ሁሉም እንደየሚናቸው የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዉ ቅሬታን የሚቀንስ፤ ብልሹ አሰራርን የሚፈታና ፍትሐዊነትን የሚያሰፍን አሠራር በማስፈን እንዲሁም በግዥና ንብረት አስተዳደር ይመጣ የነበረዉን ችግር በመቅረፍ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ በማለት ስልጠናውን አጠቃለው የቀጣይ ጊዜ ስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ስልጠናውን በአግባቡ ለተከታተሉ ሠልጣኞች በቢሮ ሃላፊው በአቶ አታላይ ጥላሁን የምስጋና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመጨረሻም የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተካሂዷል። ከአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ሊንኮች ይጠቀሙ ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/191YyDU2YK/ ዩቲዩብ http://www.youtube.com/@AmharaFinanceBureau ቴሌግራም https://t.me/AmharaBureauofFinance ዋትስአፕ https://whatsapp.com/channel/0029Vb8BHKA4SpkAKHBs6M0H ኢንስታግራም https://www.instagram.com/amhara415?igsh=MTh1Nzd3dnNpaWRxMg== ቲክቶክ https://www.tiktok.com/@amhara.finance.bureau?_r=1... ዌብሳይት http://www.amharabofec.gov.com/ ኤክስ (ትዊተር) https://twitter.com/@amhara_finance