ክልሉ የቻናል አንድ ፕሮግራሞችን ውጤታማ አድርጎ መምራት መቻሉን ቢሮው አስታወቀ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ በቻናል አንድ ፕሮግራሞች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ እየደገፉ ከአጋር አካላት ጋር እየተገመገመ መምራቱን ቢሮው አስታወቀ፡፡ በገንዘብ ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ተወካይ አስተባባሪ ወ/ሮ ሲሃም ወርቁ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች የገንዘብ ፍሰታቸው ቀጥታ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ክልል ገንዘብ ቢሮዎች እና ታች ዞንና ወረዳ መዋቅሮቻቸው ጭምር የሚመጣውን ሃብት ከባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ ቅንጅት እየተገመገመ በቀጥታ የሪፖርት እና የኦዲት ክትትል ስርዓትን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ነው ብለዋል፡፡ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ሃብት በአገራዊ ስምምነት ተደርጎበት የሚመጣ ነው ያሉት ወ/ሮ ሲሃም በክልላችን ከ 28 እስክ 30 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሃብት ተመድቦለት ማህበራዊ እና መስረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችን ትኩረት አድርጎ የሚተገብር ፕሮግራም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ችግር ውስጥ ሆኖም ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ እንደ ገንዘብ ቢሮ አብዛኛው የፋይናንስ ስርዓታችን በሲስተም በአይቤክስ ሶፍትዌርና በመሳሰሉት ስለሚተገበር በዚህ አግባብ መፈጸማችን ዘርፉን ውጤታማ አድርጎታል ያሉት ወ/ሮ ሲሃም የዞን፣የከተማና የወረዳ መዋቅሮቻችንን በአግባቡ በመጠቀም የነበሩ ችግሮችን በወቅቱ እየፈታን ውጤታማ ስራ ስረተናል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በቻናል አንድ ፕሮግራሞች የዘርፍ ተኮር የቴክኒክ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥላሁን እሸቴ በበኩላቸው በቻናል አንድ ፕሮግራሞች የሚመጣውን ሃብት የገንዘብ ቢሮ ከገንዘብ ፍሰቱ ጀምሮ ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ በስልጠና፣ በሪፖርት ግንኙነትና በአካል ግምገማ ጭምር ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከአጋር አካላትና ፕሮግራሙ ከሚፈጸምባቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮግራሙ መሰረታዊ የእድገት ተኮር ተቋማት ከሚባሉት ግብርና፣ጤና ፣ትምህርት፣ውሃና መንገድ ቢሮዎችና ታች ተዋረድ ተቋማት ጋር የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት አቶ ጥላሁን የፕሮግራሙን ሃብት ከመደበኛው በጀት ጋር አብሮ በክልሉ ትሬዥሪ እየተመራ ለክልላችን ልማት የራሱን አሰተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ከረጂ ድርጅቶች በተደረገ ስምምነት መሰረት የፕሮግራሙን ሃብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በውስጥና በውጭ ኦዲተሮች ኦዲት እየተደረገ እንደሚመራ እና አጠቃላይ የሂሳብ ፣ የግዥና መሰል ስራዎች በመንግስት የፋይናንስ ስርዓት እየተመራ መሰራቱ ፕሮግራሙን የበለጠ ውጤታማ አድርጎታል፡፡