ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ሚናቸው የጐላ እንደሆነ ተጠቆመ
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ሴት ሰራተኞች “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለፀገች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ በአገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በፓናል ውይይት አከበሩ፡፡ የገንዘብ ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አዱኛ የዕለቱን የፓናል ውይይት በመክፈት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባትላለፍበት ወቅት ሴቶች የማህበረሰቡ አንዱ አካል በመሆን በርካታ ተግባራትን ሲያከናወኑ የቆዩና በተሳትፎአቸውም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ አስተዋፅኦቸው ላቅ ያለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሴቶች ላይ የነበረውን ጭቆና በማንሳትና የፆታ እኩልነት እንዲኖርና በሰላም፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ሁሉ በመሳተፍ መልካም ተሞክሮዎች እንዲሰፋ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ም/ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ መሠረት በመክፈቻው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ቢሮ የስርአተ ፆታና ማህበራዊ ማካተት ባለሙያ ወ/ሮ አላዩ ቢተው "የ50 ዓመት የሴቶች ጉዞ "በሚል የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በሰነዱ የሴቶች ተሳትፎ ከንጉሱ ሥርዓት እስከ አሁኑ ሥርዓት የነበራቸውን ሚና እና ተሳትፎ በግልፅ አመላክተዋል። በዋናነትም ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ፣ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጭነት ፣ ጥቃትን መከላከል ላይ እና የቴክኖሎጂ ችሎታቸውን በማሳደግ በፈጠራ ሥራ አቅማቸውን መገንባት እንዳለባቸው አብራርተዋል። በመጨረሻም በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በመቀበልና ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ወ/ሮ መሠረት አዱኛ እኛ ሴቶች የሴቶችን ሁለንተናዊ እኩልነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት፣ ለሰላምና ፀጥታ ዘብ መቆም ፣ በኢኮኖሚ ራስን ማሳደግ፣ ውሳኔ ሰጭነት አቅማችን ማጎልበት እና የተጠያቂነት መርህን ማስፈን፣ እንዲሁም የሴቶችን መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ በሁሉም መስክ የሚኖረን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የግንዛቤ ፈጣሪነት እና ተጽእኖ ፈጣሪነት ሚናችንን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል በማለት ውይይቱን አጠቃለዋል።