የትብብርና አጋርነት ፎረሙ ለቀጣይ ተነሳሽነትን ያመላከተ ነበር
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በሚል መሪ ቃል በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመታዊ የአጋርነትና ትብብር ፎረም የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በትብብርና አጋርነት የበለጠ ተጠናክሮ መስራት በሚያስችል ሁኔታ ተመክሮበት ተጠናቋል፡፡ በመድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ገብተው እንዲሰሩ የሚያግዙ የጥናት ውጤቶች ቀርበው የተመከረባቸው ሲሆን በዚህ ጥናት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳይንሳዊ በሆነና በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመስርተው የክልሉን ማህበረሰብ አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአደጋ ስጋት ምላሽ ስራዎችን በአግባቡ እንዲሰሩ የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን ገልፀዋል፡፡ የአማራ ክልል ህዝብ ትንሽ ተሰርቶለት በብዙ የሚያመሰግን ውለታ የማይረሳ ትልቅ ህዝብ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው አቶ አታላይ በቻልነው አቅም ሁሉ ይህንን ህዝብ በቀናነትና በጋራ ቅንጅት ተናበን ልናገለግለው ይገባል ብለዋል፡፡ በመድረኩ በተለያዩ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እውቅና በመስጠትና የተለያዩ የአሰራር አቅጣጫዎችን ተሰጥቶበት ተጠናቋል፡፡