የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የግዥ አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ ዉይይት ተካሄደ
መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (ገንዘብ ቢሮ) በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ በተዘጋጀዉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የግዥ አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ ዉይይት ተካሂዶአል፡፡ በአማራ ብሄራዊ ክልል ም/ቤት በቅርቡ የጸደቀዉን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ተከትሎ በአዋጁ አንቀጽ 78(2) እና በክልሉ መንግስት አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ተሻሽሎ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 300/2017 ዓ.ም አንቀጽ 32 በተሰጠዉ ሥልጣን መሠረት በገንዘብ ቢሮ በተዘጋጀዉ ረቂቅ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ላይ በቢሮዉ ማኔጅመንት አባላት ዉይይት ተደርጎአል፡፡ የዉይይት መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን በረቂቅ መመሪያዉ ላይ በቢሮ ደረጃ ተገቢ ዉይይት ተደርጎ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ መደረጉ መልካም መሆኑን ገልጸዉ ለቀጣይ ይህ መመሪያ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ ዉይይት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ በየዉይይት መድረኩ የሚሰጡ ጠቃሚ ግብዓቶችም በመመሪያዉ ላይ መካተትና የተሻለ እና ዘመኑን የዋጀ መመሪያ ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡