የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀው በአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በማዳበር መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ::
የአማራ ክልል የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመታዊ የአጋርነትና የትብብር ፎረም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና የተለያዩ አጋር አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በአማራ ክልል መንግስትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የትብብርና የአጋርነት ፎረም ላይ ተገኝተው እንደገለፁት ክልሉ በሰላም እጦት ከገባበት ችግር ወጥቶ ወደ ዘላቂ ልማት እንዲገባ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው በዚህ ተግባር ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመንግስትን ክፍተት መሙላት ሳይሆን በትብብር እና አጋርነት ላይ ተመስርተው መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡ ባለፉት ሶስት እና አራት አመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልላችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚመሩበት ማዕቀፍ ዜጐችን በማሳተፍ የአገርንና የህዝብን ክብር ከፍ በማድረግ በሚያስችል ሁኔታ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ በአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በማዳበር መስራት እንደሚገባና በዚህ ተግባርም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ አታላይ ጥላሁን በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለክልሉ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሰብአዊ ድጋፍ እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች እውቅና ይሰጣል ያሉ ሲሆን እነኚህ የልማት አጋሮቻችን በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃ፣ በግብርናና በመሳሰሉት ሰፊ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ አታላይ አክለውም የልማት አጋሮቻችን ወደ እኛ አንድ እርምጃ ሲመጡ የመንግስት ተቋማት ደግሞ ወደ እነሱ ሁለት እርምጃ በመሄድ ለህዝባችን የላቀ ውጤት ማምጣት አለብን ብለዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልላችን ለሚተገበሩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት አዋጆችን በማሻሻልና የተለያዩ ፕላት ፎርሞችን በማስተካከል በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ አታላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀው በአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ለክልላችን ህዝብ ተጠቃሚነትና ልማት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡