የፕሮጀክት ሃብቶች የመንግስት የልማት እቅዶች ማስፈፀሚያ እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል ተባለ
በአብከመ ገንዘብ ቢሮ የውጭ ሃብት ግኝት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ከመደበኛ በጀት ውጭ ያሉ የእርዳታና ብድር ሃብቶችን ፕሮግራሙ ለተቀረፀለት አላማ እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የሚመጡ ሃብቶች እንደሆኑ ተገለፀ፡፡ በአብከመ ገንዘብ ቢሮ የውጭ ሃብት ግኝት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰብለወርቅ ሙላት የእርዳታና ብድር ሃብቶች ሲመጡ መረጃ ከማደራጀት ጀምሮ በአግባቡ ጥቅም ላይ ውለው ለውጥ እንዲያመጡ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ የገለፁ ሲሆን እነዚህ ሃብቶች በ3 ቻናሎች ተከፋፍለው እንደሚመጡና ቻናል አንድ ዋናውን የመንግስት ትሬዥሪ ነክተው ወደ መንግስት ቢሮዎች/ተቋማት ላይ በቀጥታ የሚመጡ ገንዘቦች ሲሆኑ የሪፖርት ግንኙነቱም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር መሆኑ፣ ቻናል 2 የገንዘብ ቢሮው ትሬዥሪ ሳይነካው ከሚኒስቴር መ/ቤቶች ቀጥታ ወደ እያንዳንዱ ተቋም የሚወርድና የገንዘብ ቢሮን ትሬዥሪ የማይነካ ሃብት እንደሆነ እና ቻናል3 የፋይናንስ አስተዳደሩም የሰው ሃይል አስተዳደሩም ራሳቸውን ችለው የሚሰሩ በሚል በሶስት መንገዶች ሃብቶች እንደሚመጡ አብራርተዋል፡፡ ወ/ሮ ሰብለወርቅ አያይዘውም ገንዘብ ቢሮ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን በመነሳት በሶስቱም ቻናሎች የሚመጡ ሃብቶችን ለመጣለት አላማና በተመደበለት የጊዜ ገደብ ስራ ላይ መዋሉን እንዲሁም ምን ያህል ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን በተዋረድ ከቢሮ እስከ ወረዳ ገንዘብ ጽ/ቤት ድረስ በስትሪንግና ቴክኒካል ኮሚቴዎች ጭምር ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራ እንደሚሰራም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ የሁለትዮሽ ግንኙነት/ባይላተራል እና ከሁለት በላይ/መልቲላተራል ግንኙነት የልማት አጋሮቻችን የአለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ አነዚህና ሌሎች በአፈርና ውሃ ጠበቃ፣ በመጠጥ ውሃ፣ በትምህር፣ በጤና ዘርፍ መስፋፋት፣ በከተሞች የመሰረተ ልማት ጥገና፣ በመልሶ መቋቋምና በእለት ደራሽ ስራዎች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁሉም ፕሮጀክቶች መነሻ የሚያደርጉት የመንግስትን የልማት እቅድ ሆኖ በመደበኛ በጀት መሸፈን የማይቻለውን በእነዚህ ፕሮግራሞች ይሸፈናል ያሉት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰብለወርቅ በፋይናንስ ብቻ ሳይሆን በቴክኒካልና እውቀትም ጭምር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡ በመጨረሻም ክልሉ ችግር ውስጥ ሆኖም የተሻለ ስራ እየተሰራ እንደሆነና በያዝነው በጀት አመት በ6 ወራት ውስጥ ለ38 ወረዳዎች አመች ባልሆነ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ድጋፍና ክትትላችን በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም ያሳየንበት ነው ሲሉ ይህም ሆኖ የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ተጨማሪ ሃብት እንዲመጣ ምቹ ሁኔታዎችን መፈጠርና የመፈፀም አቅማችንን ከፍ በማድረግ የፕሮጀክቶችን ሃብት አሟጦ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡